
ምስራቅ አርሲ እያነባች ነው! የኢሰመጉ 158ኛ ልዩ ሪፖርት የገለጠው መራር እውነታ!
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) “158ኛ ልዩ ሪፖርት፡ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ስለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች” (ሐምሌ 2026 / ጁላይ 2026፣ አዲስ አበባ)
መግቢያ
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ ዞን ውስጥ ለዘመናት በጋራ፣ በጋብቻ እና በማህበራዊ ትስስር ተሳስረው የኖሩ የተለያዩ ብሔር እና ሃይማኖት ተከታይ ማህበረሰቦች ይገኛሉ። አብዛኞቹ በእርሻ ስራ የሚተዳደሩ፣ ሰላማዊ ኑሮን የመረጡ ዜጎች ናቸው። ይሁን እንጂ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በዚህ አካባቢ ንጹሃን ዜጎችን ኢላማ ያደረጉ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ በቅርቡ ባወጣው 158ኛ ልዩ ሪፖርቱ በምስራቅ አርሲ ዞን በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች – ሽርካ፣ መርቲ፣ ጅጅ፣ አርሲ ሲሬ፣ ሮቤ፣ ሙኒሳ፣ ጉና፣ ሆንቆሎ ዋቤ እና አሴቆ – ከ2014 ዓ.ም. እስከ 2018 ዓ.ም. ግንቦት ወር ድረስ ስለተፈጸሙ ግድያዎች፣ አካላዊ ጉዳቶች፣ አፈናዎች፣ መፈናቀሎች እና የንብረት ውድመቶች ዝርዝር መረጃ ይፋ አድርጓል። ይህ ጽሑፍ በዚያ ሪፖርት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ማጠቃለያ ነው።
የምርመራው ዘዴ እና ዳራ
ኢሰመጉ ከመጋቢት 3 እስከ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. ባለሙያዎቹን ወደ ተጠቀሱት ወረዳዎች በማሰማራት ምርመራ አካሂዷል። መርማሪዎቹ ከሟቾች ቤተሰቦች፣ ከተጎጂዎች፣ ከዓይን እማኞች ጋር ቃለ-መጠይቅ በማድረግ፣ የአርሲ ሀገረ ስብከትና የየወረዳ ቤተ ክርስቲያን ጽ/ቤቶችን በማነጋገር፣ እንዲሁም ማስረጃ ሰነዶችን በመመልከትና በመስክ ምልከታ መረጃውን አሰባስበዋል።
ድርጅቱ ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምስራቅ አርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያ፣ ለምስራቅ አርሲ ዞን እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት እና ለኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ደብዳቤ ልኮ መረጃ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም፣ ሪፖርቱ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ከየትኛውም አካል ምላሽ አላገኘም። ከዚህ ባለፈ ምርመራው በራሱ ቀላል አልነበረም፤ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት የመጓጓዣ ችግር፣ ፍርሃት ውስጥ ያሉ ተጎጂዎች መረጃ ለመስጠት ያለመፍቀድ፣ እንዲሁም ተጎጂዎች ተበታትነው በመሰደዳቸው ማግኘት አዳጋች መሆኑ የምርመራውን ስራ ፈታኝ አድርገውታል።
“የተኩስ ድምጽ ስንሰማ ቤተሰቦቻችን ወደ ጫካ ተበታተኑ“
ሪፖርቱ ካካተታቸው ምስክርነቶች መካከል የአንድ ቤተሰብ አባል የተናገረችው ይገኝበታል። ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት ላይ የታጠቁ ኃይሎች ቤቷን ከበው አባቷን፣ ሁለት አጎቶቿን እና የአጎቷን ልጅ ወሰዱ። ሴቶችና ህጻናት ተትተው ወንዶች ብቻ ተወሰዱ። የተኩስ ድምጽ ሲሰሙ የቀሩት ቤተሰቦች ወደ ጫካ ተበታተኑ። በዚያች ሌሊት የአጎቷና የአጎቷ ልጅ አስከሬን ተገኘ። ቀሪዎቹ በህይወት እንዳሉ በስልክ ተነግሯቸው፣ ቀጥሎም 1,000,000 ብር ካሳ እንዲከፈል ተጠየቁ። ቤተሰቡ 750,000 ብር ሰብስቦ ቢያስረክብም፣ ከቀናት በኋላ የተያዙት ሰዎች አስከሬን በሌላ ወረዳ ተጣለ ተብሎ ተነገራቸው። ይህ የአንድ ቤተሰብ ታሪክ ብቻ ሲሆን፣ በሪፖርቱ ውስጥ ተመሳሳይ ስቃይ ያሳለፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ስም ዝርዝር ተመዝግቧል።
የግድያ አሃዞች፡ ስም–ዝርዝር የያዘ ማስረጃ
ኢሰመጉ ከ2014 ዓ.ም. እስከ መስከረም 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ባሰባሰበው መረጃ መሰረት፣ በርካታ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ህይወታቸውን አጥተዋል፦
- ሽርካ ወረዳ፦ 116 ሰዎች
- መርቲ ወረዳ፦ 117 ሰዎች
- ጅጅ ወረዳ፦ 101 ሰዎች
- ሮቤ ወረዳ፦ 47 ሰዎች
- ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ፦ 20 ሰዎች
- ሙኒሳ ወረዳ፦ 19 ሰዎች
- ጉና ወረዳ፦ 26 ሰዎች (ከእነዚህ ውስጥ 16ቱ የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በናኖ ጃዊ ቀበሌ ተገድለው፣ 5ቱ በአንድ ጉድጓድ በነገሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተቀብረዋል)
- አርሲ ሲሬ ወረዳ፦ 3 ሰዎች
- አሴቆ ወረዳ፦ 5 ሰዎች
በተጨማሪም የአካባቢውን ሰላም ሲጠብቁ የነበሩ 4 የአካባቢ ታጣቂ (ሚሊሺያ) አባላት በአሴቆ ወረዳ ተገድለዋል። በጠቅላላው በሪፖርቱ ውስጥ በስም ከተዘረዘሩት ብቻ ከ450 በላይ ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ብዙዎቹ አረጋውያን፣ ሴቶች እና ህጻናት ጭምር ናቸው። ከተጎጂዎቹ መካከል ገና 15 እና 16 ዓመት የሞላቸው ወጣቶች፣ እንዲሁም ከ4 አመት እድሜ ጀምሮ ያሉ ህጻናት ይገኙበታል።
ሪፖርቱ በአባሪነት ያካተታቸው ፎቶግራፎች የተገደሉትን ሰዎች የፊት ገጽታ ያሳያሉ – ከእነዚህ መካከል በአንድ ቀን የሞቱ ሙሉ ቤተሰቦች ፎቶዎች ይገኙበታል፤ አባት፣ እናት፣ ልጆች እና የልጅ ልጆች በጋራ የተቀበሩበት ሁኔታ ልብ የሚሰብር ነው።
አካላዊ ጉዳት፡ የህጻናት ስቃይ
ከግድያ በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ከባድ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሪፖርቱ በጉና ወረዳ የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. የተፈጸመውን አንድ አሰቃቂ ክስተት ይተርካል፦ የታጠቁ ቡድኖች ወደ አንድ ቤተሰብ ቤት ገብተው ምግብና መጠጥ ጠይቀው ካሳለፉ በኋላ፣ በዚያች ሌሊት 6 ሰዎችን፣ በማግስቱም 10 ተጨማሪ ሰዎችን ወደ ጫካ ወሰዱ። ከተወሰዱት 16 ሰዎች መካከል 14ቱ ተገድለው፣ የ4 እና የ8 ዓመት እድሜ ያላቸው ሁለት ህጻናት ተተኩሶባቸው በህይወት ተርፈው ነበር። የ8 ዓመቷ ህጻን በአምስት ቦታ ተመትታ የተረፈች ሲሆን፣ የ4 ዓመቱ ህጻን በሁለት ጥይት ተመትቶ የግራ እግሩ ተቆርጦ ጠፍቷል።
አፈና እና ጠለፋ
የታጠቁ ኃይሎች በሃይማኖት ላይ ተመስርተው ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ሰዎችን ሲያፍኑ እንደነበር ሪፖርቱ ያመለክታል፦
- ሮቤ ወረዳ፦ 156 ሰዎች ታፍነው፣ 141ኙ ተለቀዋል፣ 15ቱ አሁንም የደረሱበት አልታወቀም
- ጅጅ ወረዳ፦ 182 ሰዎች (166 ወንዶች እና 16 ሴቶች) ገንዘብ ተከፍሎ ተለቀዋል
- መርቲ ወረዳ፦ 29 ሰዎች ታፍነው፣ 27ቱ ገንዘብ ተከፍሎ ተለቀዋል፤ አንድ ባልና ሚስት ከንብረታቸው ጋር አሁንም ጠፍተዋል
- ሙኒሳ ወረዳ፦ 2 ሰዎች ታፍነው የደረሱበት አልታወቀም
- ሽርካ ወረዳ፦ 39 ሰዎች ታፍነው ሁኔታቸው እስከ ሪፖርቱ ዝግጅት ጊዜ ድረስ አልታወቀም
ከሽርካ ወረዳ የተወሰዱ ቤተሰቦች እንደገለጹት፣ ታፋኞቹ ገንዘብ ከተከፈለ በኋላም አልተለቀቁም። ያመለጠ አንድ ተጎጂ እንደመሰከረው፣ ታፋኞቹ ወደ ወንዝ ዳርቻ ተወስደው በሆዳቸው ተኝተው እንዲገደሉ ሲታዘዙ፣ ከመተኛት ይልቅ ሮጦ ማምለጡን ተናግሯል፤ ጥይት ሲተኮስበት በማምለጡ ቢተርፍም የተቀሩት ወገኖቹ እጣ ፈንታ ግን እስከ ዛሬም አልታወቀም። ሁለት ዓመታት ካለፉ በኋላም ቤተሰቡ የወዳጆቻቸውን ህይወት ወይም ሞት ማወቅ አልቻለም።
ሌላ የ60 ዓመት አዛውንት ደግሞ ታፍኖ ስድስት ቀናት በጫካ ውስጥ ከቆየ በኋላ 500,000 ብር ተከፍሎለት እንደተለቀቀ፣ በእስር ወቅት ጭንቅላቱ ላይ በጩቤ ተመትቶ እንደተጎዳና እስከ ዛሬም ህመሙ እንደቀጠለበት ገልጿል።
መፈናቀል፡ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ቤተሰቦች
ላለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ለደረሰባቸው ግድያ፣ አካላዊ ጉዳት፣ አፈናና የንብረት ውድመት ዘላቂ መፍትሔ ባለማግኘታቸው፣ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል። በተለይ ሴቶችና ህጻናት ለከፍተኛ ተጋላጭነት ተዳርገዋል። ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም. ድረስ በምስራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት መረጃ መሰረት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እንደሚከተለው ነው፦
- ጅጅ ወረዳ፦ 6,216 ሰዎች (3,310 ወንዶች እና 2,906 ሴቶች)
- ሽርካ ወረዳ፦ 3,746 ሰዎች
- አሴቆ ወረዳ፦ 2,133 ሰዎች
- ሮቤ ወረዳ፦ 1,270 ሰዎች
- መርቲ ወረዳ፦ 1,036 ሰዎች
- ሙኒሳ ወረዳ፦ 29 ሰዎች
- ጉና ወረዳ፦ 21 ሰዎች
በጠቅላላ ከ14,000 በላይ ወገኖቻችን ከቀያቸው ተፈናቅለው በሌላ ስፍራ በስደት ህይወት ውስጥ ይገኛሉ።
የንብረት ውድመት እና የተቃጠሉ ቤተ ክርስቲያናት
ሪፖርቱ በተጨማሪ በሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ የንብረት ውድመትን ይዘረዝራል፦
- ጅጅ ወረዳ፦ ብዙ ከብቶችና የጭነት እንስሳት ተዘርፈዋል፤ 5 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል፤ 62 ቤቶች ፈርሰዋል፤ ሙካ ጉራቻ ቅድስት ማርያም እና ጉሬ ጣቢኖ ቅዱስ ገብርኤል/መድሃኒዓለም ቤተ ክርስቲያናት ተዘርፈዋል፤ አርጆ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተልሔም ፈርሷል፤ በፍርሃትና በመፈናቀል ምክንያት 8 አብያተ ክርስቲያናት ለመዘጋት ተገደዋል። መሬታቸው ላለፉት 3 ዓመታት ባይታረስም ማህበረሰቡ የመሬት ግብር መክፈሉን ቀጥሏል።
- ሮቤ ወረዳ፦ 8 ቤቶች ተቃጥለዋል፤ 235 ከብቶች ተዘርፈዋል፤ በግምት ወደ 10 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ንብረት ወድሟል።
- አሴቆ ወረዳ፦ የ101 ዓመት እድሜ ያለው የተለታ ጨፋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተዘርፎ ተቃጥሏል።
ህጋዊ መሰረት፦ ይህ ምንድን ነው?
ኢሰመጉ ሪፖርቱ የፌዴራል ህገ መንግስት አንቀጽ 14፣ 15፣ 16 እና 27ን፣ እንዲሁም አለም አቀፍ ሰነዶች – የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን፣ የአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝቦች መብቶች ቻርተር፣ እና የሮም ቻርተርን – ጠቅሶ የተፈጸሙት ድርጊቶች የህይወት፣ የአካል ደህንነት እና የሃይማኖት ነጻነት መብቶችን የሚጥሱ መሆናቸውን ያስረዳል።
በተለይ ትኩረት የሚስበው ክፍል፣ ሪፖርቱ ጥቃቶቹ በስፋትና በስርዓት (widespread and systematic) በሲቪል ህዝብ ላይ የተፈጸሙ በመሆናቸው፣ በአለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (ICC) የሮም ቻርተር አንቀጽ 7 መሰረት የሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች (Crimes Against Humanity) አመላካቾችን ሊያሟሉ እንደሚችሉ የሚያመለክት መሆኑ ነው። ሪፖርቱ እንደሚያብራራው፣ ተጎጂዎቹ ያልታጠቁ ሲቪል ዜጎች ሲሆኑ፣ ጥቃቱ ደግሞ በተደራጀ እና ተደጋጋሚ ሁኔታ የተፈጸመ ነው።
የኢሰመጉ ጥሪ
ኢሰመጉ በሪፖርቱ መደምደሚያ ላይ የሚከተሉትን ጥሪዎች አቅርቧል፦
- የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል መንግስታት በሃይማኖትና በማንነት ላይ ተመስርተው ጥቃት የፈጸሙ ታጣቂዎችን፣ እንዲሁም ግዴታቸውን ባለመወጣት የሚጠየቁ የጸጥታ ሃላፊዎችን በአስቸኳይ ለፍትህ እንዲያቀርቡ፤
- የኦሮሚያ ክልል መንግስት በምስራቅ አርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን ፈጻሚዎች በሙሉ ተከታትሎ ለፍርድ እንዲያቀርብ፤
- ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደረግ፣ በክብር እና በደህንነት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የማህበረሰብ ውይይት በማካሄድ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር፤
- ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው ፈጣን ፍትህ፣ በቂ ካሳ እና የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲሰጥ፤
- የኦሮሚያ ክልል መንግስት ጥቃቶቹን መቆጣጠር ካልቻለ፣ የፌዴራል መንግስት በህገ መንግስቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ጣልቃ ገብቶ የዜጎችን የህይወት መብት እንዲያስጠብቅ።
መደምደሚያ
የምስራቅ አርሲ ዞን ታሪክ የብዙ ቤተሰቦችን እንባ፣ የብዙ ልጆችን ወላጅ-አልባነት፣ እና የብዙ አዛውንት እናቶችንና አባቶችን ሞት በጥቂቱም ቢሆን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚገልጽ ማስረጃ ነው። ይህ ሪፖርት ከቁጥር ባሻገር፣ የንጹሃን ዜጎችን ጭፍጨፋ እና እልቂት ታሪኮችን ይዟል። ከ450 በላይ የተገደሉ ወገኖቻችን፣ ከ14,000 በላይ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታፍነው ደረሳቸው ያልታወቀ ወገኖቻችን – እነዚህ ሁሉ ቁጥሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ የሰው ልጅ ህይወት፣ የቤተሰብ ትስስር፣ የማህበረሰብ ታሪክ መጥፋት የሚያሳቱ መግለጫዎች ናቸው።
በኔዘርላንድስ የምንኖር የአማራ ማህበረሰብ አባላት ሆነን፣ ከሀገራችን ርቀን ብንኖርም ልባችን ግን ከዚያ ምድር ካሉ ወገኖቻችን ጋር ነው። ይህን ሪፖርት በስፋት በማሰራጨት፣ ድምጻቸው ለተነፈጉ ወገኖቻችን ድምጽ በመሆን፣ ለፍትህ፣ ለተጠያቂነት እና ለዘላቂ ሰላም የበኩላችንን ልናደርግ ይገባል። ዝምታ የበለጠ ጥቃት እንዲቀጥል እድል ከመስጠት ውጪ ምንም አይፈይድም።
ይህ ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) “158ኛ ልዩ ሪፖርት” ላይ የተመሰረተ ማጠቃለያ ነው። ሙሉውን ሪፖርት፣ ተጨማሪ ስም ዝርዝሮችን፣ ፎቶግራፎችን እና ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት www.ehrco.org የድርጅቱን ድረ–ገጽ ይመልከቱ፣ ወይም ኢሰመጉን በኢሜይል info@ehrco.org ያግኙ።
