
ከአማራ ማህበር በኔዘርላንድ የአፋብን ምስረታ አስመልክቶ የተሰጠ የድጋፍ እና የደስታ መግለጫ
የአማራን ህዝብ በጠላትነት እና በአጥቂነት የሚፈርጅ እና በጥላቻ-ተኮር የሃሰት ትርክቶች ላይ የተመረኮዘ ፖለቲካዊ ስርዓት መምጣቱን ተከትሎ መላው የአማራ ህዝብ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ለሁለንተናዊ ስርዓት-መር ጥቃቶች እና ጭቆናዎች መጋለጡ በአደባባይ የተገለጠ እውነት ነው። በአማራ ህዝብ ላይ የተከፈተውም መንግስት-መር ጥቃት ከእለት ተለት አስተዳደራዊ መድሎ እስከ ህልውና ስጋት ድረስ የተዘረጋ መሆኑ ይታወቃል።ይህንንም በመረዳት እና የተደቀነውንም የህልውና ስጋት ለመቀልበስ ያለሙ ተናጠላዊ እና ቡድናዊ ትግሎች በአማራ የቁርጥ ቀን ልጆች ሲደርጉ ቆይተዋል። ሆኖም ግን ጥቃቱ እና የህልውና ስጋቱ እየተባባሰ ከመሄዱ ባሻገር በፖለቲካዊ አደረጃጀቶች እና ቀድመው በነቁ የአማራ ልጆች ሲደረጉ የቆዩት የትግል ስልቶች የተፈልገውን ሁሉን አቀፍ ድል ማስመዘገብ አልቻሉም ነበር።የአማራ ህዝብ ከማንነት ተኮር የግለስብ ግድያ እስከ ጅምላ ጭፍጨፋ፣ የዘር ማጥፋት፣ የጅምላ እስር፣ የጦር ወንጀል ፣ ወረራ ፣ ርሃብን እና ጾታዊ ጥቃትን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም ፣ ማፈናቀል ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ስነልቦናዊ እና ባህላዊ ጥቃቶች… ወዘተ እየተፈጸመበት ቀጥሏል። በዚህ ምክንያትም መላው የአማራ ህዝብ በተናጥል እና በቡድን ትግሎችን ሲያደርግ ቆይቷል። እኛም በኔዘርላንድስ ሃገር የምንኖር አማራዎች እና ጉዳዩ ይመለከተናል ያልን ነዋሪዎች በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን መንግስት-መር ሁሉን አቀፍ ጥቃት እና ሰቆቃ እንዲቆም በኔዘርላንድ እና በሌሎች የአውሮፓ ከተሞች በተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ስናዘጋጅ እና ስንሳተፍ ከመቆየታችንም በተጨማሪ በሃገር ቤት የሚገኙ ተጎጂ ወገኖቻችንን በምንችለው አቅም ለመደግፍ ጥረቶችን ስናደርግ ቆይተናል።እንዳለመታደል ሆኖ በአማራ ህዝብ ላይ እየደርሰ ያለውን መዋቅራዊ እና ስርዓት-መር ጥቃት እና የህልውና አደጋ መቀልበስ የሚያስችሉ ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ አማራጭ በሮች በሙሉ የተዘጉ በመሆናቸው እና ተሞክረውም በመክሸፋቸው የትጥቅ ትግል ጥቅም ላይ የሚውል ብቸኛው የትግል መሳሪያ ሆኖ መምጣቱን ማህበራችን ይገነዘባል።የአማራ ህዝብ ከዚህ አደጋ ለመውጣት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሰፊ የማህብረሰብ ድጋፎችን እና ድሎችን እያስመዘገበ የመጣ ቢሆንም ከዚህ ቀደም የነበረው የአማራ ትግል ወጥነት እና ተቋማዊ አንድነት የጎደለው ሆኖ ቆይቷል።ይህንንም ተከትሎ በአማራ ትግል አመራሮች፣ አባላት ፣ ደጋፊዎች እንዲሁም በመላው የአማራ ህዝብ እና የኢትዮጵያ መጻዒ እድል በሚያሳስባቸው ወገኖች የአንድነት ጥሪዎች እና ውትወታዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል። በመሆኑም የህዝባቸውን፣ የአባላቶቻቸውን እና የደጋፊዎችቻውን ድምጽ በመስማት እንዲሁም የአንድነቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እና እጅግ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ከቀን 09/05/ 2018 ዓ.ም ጀመሮ የአማራ ህዝብ ትግል በአንድነት እና በወጥነት የሚመራበት ተቋማዊ አሰራር እና ትግሉን የሚመራ ድርጅት በይፋ ተበስሯል። ይህንንም ተከትሎ የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በአማራ ህዝብ ላይ የተደቀነውን የህልውና ስጋት ለመቀልበስ እና ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ በማምጣት የእኩል እድል ተጠቃሚነት፣ ፍትህ፣ ነጻነት እና የህግ የበላይነት የተረጋገጡባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን የማድረጉን ትግል የሚመራ ድርጅት ሆኖ ተወልዷል።ለዚህም የመጀመሪያው ምዕራፍ አኩሪ ድል የአማራ ማህበር በኔዘርላንድ አባላት ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል። የአንድነት መድረኩ ሁሉንም አማራ በእኩልነት እና በአንድነት ያቀፈ ሆኖ እንዲቀጥል ሁሉም የድርሻውን ገንቢ ሚና እንዲጫዎት ጥሪ በማስተላለፍ ይህም እንዲሳካ የበኩላችሁን አወንታዊ ሚና ለተወጣችሁ የህዝብ ልጆች ታላቅ ምስጋናችንን እያቀርብን ፥ አዲሱ የትግል አንድነት ከግለሰቦች ሽኩቻ የጸዳ ፥ ግልጽነት እና ተጠያቂነት የሰፈነበት እና ከግል እና የቡድን ፍላጎቶች ይልቅ የተከበረውን የአማራ ህዝብ ያማከለ እንዲሆን በማሳሰብ ውህደቱን በሙሉ ልባችን የምንደግፈው መሆኑን በታላቅ አክብሮት ለመግለጽ እንወዳለን።
የአማራ ማህበር በኔዘርላንድ
ድል ለአማራ ህዝብ
